ሰኞ፣ ጥቅምት 13
ይሖዋ . . . የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
አልፎ አልፎ ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የምንታገል ከሆነ አንድ እውነታ እናስታውስ፤ ይሖዋን እያገለገልን ያለነው እሱ ራሱ ስለሳበን ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛ እንኳ እንዳለን የማናውቀውን መልካም ነገር በውስጣችን አይቷል፤ ልባችንንም ያውቃል። (2 ዜና 6:30) ስለዚህ በፊቱ ውድ እንደሆንን ሲነግረን ልናምነው ይገባል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) አንዳንዶቻችን እውነትን ከመስማታችን በፊት ባደረግናቸው ነገሮች የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት ይደቁሰን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3) ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። አንተስ ልብህ እየኮነነህ ይሆን? ከሆነ አይዞህ፤ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ታግለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላሉበት ድክመቶች ሲያስብ ስሜቱ ተደቁሶ ነበር። (ሮም 7:24) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ተጠምቋል። ያም ቢሆን ስለ ራሱ ሲናገር “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” እንዲሁም “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮ. 15:9፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w24.03 27 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14
የይሖዋን ቤት [ተዉ]።—2 ዜና 24:18
ንጉሥ ኢዮዓስ ካደረገው መጥፎ ውሳኔ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ጓደኞችን መምረጥ እንዳለብን ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ጓደኛ የምናደርገው የግድ እኩዮቻችንን መሆን የለበትም። ኢዮዓስ ከጓደኛው ከዮዳሄ በዕድሜ በጣም ያንስ እንደነበር አስታውስ። ጓደኛ አድርገህ ከምትመርጣቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት እንዳጠናክር ይረዱኛል? በአምላክ መሥፈርቶች እንድመራ ያበረታቱኛል? ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ያወራሉ? ለአምላክ መሥፈርቶች አክብሮት ያሳያሉ? የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነገር ብቻ ነው ወይስ ትክክል ያልሆነ ነገር ሳደርግ በድፍረት እርማት ይሰጡኛል?’ (ምሳሌ 27:5, 6, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞችህ ይሖዋን የማይወዱ ከሆነ ለአንተም አይበጁህም። ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ካሉህ ግን አጥብቀህ ያዛቸው፤ ይጠቅሙሃል!—ምሳሌ 13:20፤ w23.09 9 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ጥቅምት 15
እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ።—ራእይ 1:8
“አልፋ” የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ፊደል፣ “ኦሜጋ” ደግሞ የመጨረሻው ፊደል ነው። ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ማለቱ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር እንደሚያደርሰው ያመለክታል። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍ. 1:28) በዚህ ወቅት ይሖዋ “አልፋ” እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን የሚሞሉበትና ገነት የሚያደርጉበት ጊዜ እንደሚመጣ በግልጽ ተናግሯል። ወደፊት ይህ ዓላማው ሲፈጸም ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ኦሜጋ” ይላል። ይሖዋ “ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ” የመፍጠሩን ሥራ ሲያጠናቅቅ አንድ ዋስትና ሰጥቷል። ለሰዎችና ለምድር ያወጣው ዓላማ በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና ሰጠ። በሰባተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።—ዘፍ. 2:1-3፤ w23.11 5 አን. 13-14