እሁድ፣ ጥቅምት 12
[ይሖዋ] ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
የአምላክ ቃል ታማኝ ሰዎች ጠንካራ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና በጣም ጠንካራ የሆኑት የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ጠንካራ እንዳልሆኑ የተሰማቸው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ‘እንደ ተራራ ጠንካራ’ እንደሆነ ተሰምቶት ያውቃል፤ ሆኖም ‘የተሸበረበት’ ጊዜም አለ። (መዝ. 30:7) መንፈስ ቅዱስ ለሳምሶን ለየት ያለ ጥንካሬ ሰጥቶታል፤ ያም ቢሆን አምላክ ኃይል ባይሰጠው ኖሮ ‘አቅም እንደማይኖረውና እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እንደሚሆን’ ያውቅ ነበር። (መሳ. 14:5, 6፤ 16:17) እነዚህ ታማኝ ሰዎች ጠንካራ ሊሆኑ የቻሉት ይሖዋ ኃይል ስለሰጣቸው ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እሱም ከይሖዋ ኃይል ማግኘት እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮ. 12:9, 10) ከጤና ችግሮች ጋር ይታገል ነበር። (ገላ. 4:13, 14) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የከበደው ጊዜም አለ። (ሮም 7:18, 19) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይጨነቅና ስጋት ያድርበት ነበር። (2 ቆሮ. 1:8, 9) ያም ቢሆን ጳውሎስ ሲደክም ያን ጊዜ ብርቱ ሆኗል። እንዴት? ይሖዋ ለጳውሎስ የጎደለውን ኃይል ስለሰጠው ነው። ጳውሎስን አጠንክሮታል። w23.10 12 አን. 1-2
ሰኞ፣ ጥቅምት 13
ይሖዋ . . . የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
አልፎ አልፎ ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የምንታገል ከሆነ አንድ እውነታ እናስታውስ፤ ይሖዋን እያገለገልን ያለነው እሱ ራሱ ስለሳበን ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛ እንኳ እንዳለን የማናውቀውን መልካም ነገር በውስጣችን አይቷል፤ ልባችንንም ያውቃል። (2 ዜና 6:30) ስለዚህ በፊቱ ውድ እንደሆንን ሲነግረን ልናምነው ይገባል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) አንዳንዶቻችን እውነትን ከመስማታችን በፊት ባደረግናቸው ነገሮች የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት ይደቁሰን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3) ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። አንተስ ልብህ እየኮነነህ ይሆን? ከሆነ አይዞህ፤ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ታግለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላሉበት ድክመቶች ሲያስብ ስሜቱ ተደቁሶ ነበር። (ሮም 7:24) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ተጠምቋል። ያም ቢሆን ስለ ራሱ ሲናገር “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” እንዲሁም “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮ. 15:9፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w24.03 27 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14
የይሖዋን ቤት [ተዉ]።—2 ዜና 24:18
ንጉሥ ኢዮዓስ ካደረገው መጥፎ ውሳኔ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ጓደኞችን መምረጥ እንዳለብን ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ጓደኛ የምናደርገው የግድ እኩዮቻችንን መሆን የለበትም። ኢዮዓስ ከጓደኛው ከዮዳሄ በዕድሜ በጣም ያንስ እንደነበር አስታውስ። ጓደኛ አድርገህ ከምትመርጣቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት እንዳጠናክር ይረዱኛል? በአምላክ መሥፈርቶች እንድመራ ያበረታቱኛል? ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ያወራሉ? ለአምላክ መሥፈርቶች አክብሮት ያሳያሉ? የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነገር ብቻ ነው ወይስ ትክክል ያልሆነ ነገር ሳደርግ በድፍረት እርማት ይሰጡኛል?’ (ምሳሌ 27:5, 6, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞችህ ይሖዋን የማይወዱ ከሆነ ለአንተም አይበጁህም። ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ካሉህ ግን አጥብቀህ ያዛቸው፤ ይጠቅሙሃል!—ምሳሌ 13:20፤ w23.09 9 አን. 6-7